Friday, November 29, 2013

To You - My Brother - ይድረስ

"Injustice anywhere is a threat to justice everywhere…”

ይድረስ :-
ለአንተ ለወንድሜ
በምእራቡ ወጋገን
ከድሎት ኮረብታ ቆሜ

የተዘለፈ ፊትህን
የጎደፈ ማንነትህን
እንደ ድርሳነ-ቅዱሳን
በፌስ ቡክ - በድሬ ትዩብ
... ስንክሳረ-ልሳን
አሳርህን እያየሁኝ
በከንፈር ምጥጫ በቀር - ከወሬ ወግ ያልዘለቅሁኝ
ከመፈክር ያላለፈ - ቅስር ጣቴን እየጠቆምኩኝ
በድንዛዜ ያለሁኝ...
***
ክፉ ክርፋት ቀልቤን ሰርቆ...
እንደ ሳጥናኤል መቅደስ ዕጣን
የሃዘን ጭጋግ አልብሶኝ
ነፍሴ ላይ እንዳለው ስልጣን
ግራ መግባት እየናጠኝ
እንደ ቀትረ-ቀሊል ጉንፋን...

ይድረስ ላንተ ለወገኔ
በአረብ ከርሰ-ምድር ላይ - በጣር ለጣለህ ጠኔ
መልክህን ለዋጠው ትቢያ
ከከረን ጫፍ - ከወልዲያ
ከኢትዮጵያ - እስከ- አረቢያ
ከቀይ-ባህር ምፅዋ ዳር
ከግብፅ በረሃ ጣር
“ባለ-ኤጀንት አንተን መሳይ”
ወገን ሸጦህ በአደባባይ
ገንዘብህን ለባሪያ ፈንጋይ
ተስፋህን ለአረብ ብካይ
ምኞትህን ውሃ ላይ ጣይ...
ዛሬን አዘንኩልህ ባይ!!!

የምህረት አምላክ ከተፋህ
ድህነት ከቀይ መንደርህ
ካፈናቀለ- ከጣለህ
ይድረስ ለአንተ ለወንድሜ
ህመም ጣርህን ታምሜ
በሲቃህ ከማስለምለሜ
ሞቼ ከማገገሜ
አፌ በቀር
አልታመምኩምና እኔ
ሰው መግፋት የባህል ሳለ
መጥኔ ለባባው ሆዴ
መጥኔ ለራራው ጎኔ
ነግሶ አየሁና ኩነኔ!!!

***
 
ይድረስ :-
ለእህቴ ላንቺም
በሰፈር ባደባባዩ - ከአይኔ ግርጌ ባትርቂም
በየኤርፖርቱ ሰልፍሽን
በፌስታል ቋጥረሽ ተስፋሽን
የትውልድ ወግ ህልምሽን
የነገ ጠዋት ማለዳሽን
ስትገፊ ስትለፊ
በንቀት እንዳላለፍሁሽ
ዛሬን - ጎስቁለሽ አየሁሽ???

በራሴ ምድር እየኖርኩ
በራሴ ቆዳ ደስታ
የማየውን ያላከበርኩ
በራሴ ዘብ ያልተከበርኩ
በራሴ መንግስት ያልተጠበቅሁ
አንገት መስበር ነገር በቀር
በራስ ክብሬ ያልደመቅኩ
ዛሬን በባእድ ምድር
መከበርን እንዴት ናፈቅኩ???

ጳዝዮን - ኖቨምበር 2013

"Injustice anywhere is a threat to justice everywhere. We are caught in an inescapable network of mutuality, tied in a single garment of destiny. Whatever affects one directly, affects all indirectly." ~ Martin Luther King

In reflecting to the atrocious events that I observed in the Middle East lately, I kept asking what my role is and what the perceived solution to this awful complex issue could be…

While trying to calm my boiling blood, I noted that the real solution begins when each citizen begins respecting his/her neighbor at home – on the motherland.  Without citizens respect each other, without government’s respect and treatment of its citizens with dignity, blind finger pointing and holding “others” fully accountable is pure hypocrisy!!!

RESPECT the person you see next to you TODAY!!!

Pazion     

http://www.scribd.com/doc/188075328/ToYou-MyBrother                                                 

Friday, November 1, 2013

Friday, June 28, 2013

when I love you ( ስወድሽ )ስወድሽ

ስወድሽ ፣ ስወድሽ፣ ስወድሽ
ስወድሽ  - ዋልኩና
ከነፍስሽ ተጣምራ የነፍሴ ህልውና
መልህቄ ሆነሽኝ መቆሜ እየጸና
ከውሽንፍ ጥላ ከሃሩር ዳመና
ለእግሬ ጉልበት ሆነሽ በኔ አውራ ጎዳና
ለልቤም መጽናናት ላሳቤም ጽሞና
ከፈገግታሽ ስጠግብ - በፍቅርሸ ስጽናና
ደስታሸ ብርታት ሆኖኝ ከሴቱዋም ፈተና
ከአለምሽ ስመስል ከመኖርሽ ዝና
ሳልደብቅ ነግሬሽ የውስጤን ገመና
ስወድሽ ሰንብቼ ሳፈቅርሽ ኖርኩና
ከውስጤ አገኘሁሽ ልቤን ሰረቅሽና

ጳዝዮን - re-written - ሰኔ 2013

------------------------------------

 

Till the end of time ( ከዘላለም በኋላ )ከዘላለም በኋላ …

የተቆጠሩ ቀናቶች በጊዜ ስፍር የተሞሉ
የኔ -ያንቺ ደቂቃዎች በዘመን የተከለሉ
ውስን ሰውነታችን ገደብን ቢያውጅብንም
እኔ እና አንቺ
ለመለየት አልመጣንም
ለመሞት አልተመደብንም
-----
እኔ ግን - አንቺ ግን
ይኼ “ግዜ” “አሁን” እንኳን
ዛሬነት ቢያልፍም ተጣድፎ
የትውልድ ዓይን እንደ ወግ - በጊዜ ሽንፈት ሸክፎ
እንኖር የለ ? ዘመን ዘልቆ - ፍጥረት አልፎ?

ፍቅር -
ከዚህም ዘመን በኋላ - እኛም ካለፍን በኋላ
“የባከነ -ሰዓት” ተጨምሮ - ጊዜ አቅሙ እስኪላላ
ሁሌም እወድሻለሁ - በማይለወጥ መሃላ …

ጳዝዮን - ሰኔ 2013

----------------------------------------------------

 

My Heart Beat ( ልቤ ልቤን)


ልቤ ልቤ
 

ፍቅር -
አብረን መሆን እያማረን
አብረን ውለን አብረን አድረን
የፍቅር አምላክ በባርኮቱ - ከምህረቱ ከቸረን
አብረን ኑረን
አብረን ሆነን
ኑረን ኑረን
ኑረን ኑረን - እስክንሞት
ልቤ ተንሰፈሰፈች - መንጥቃ እንዳትሄድ ፈራሁ
ነፍሴም ካንቺ ዘንድ ከርማ - እንዳትዘነጋኝ ስጋት ሰጋሁ

ልቤ በእስትንፋንሴ - ከውስጤም በሚወጣ ወላፈን
እንዳትተን እፈራለሁ- የፍቅር ዋዕይ ሲገርፈን…

ጳዝዮን - ሰኔ 2013


Followers